AmharicNewsPolitics

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ እርስበርስ መወነጃጀል

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በጠብአጫርነት እርስበርስ እየተወነጃጀሉ ነው።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በጠብአጫርነት እርስበርስ እየተወነጃጀሉ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እየጣሰችና ግጭት ለመቀስቀስ እየተንቀሳቀሰች ነው በማለት ለተለያዩ ሀገራት ደብዳቤ ጽፏል።

የኤርትራ መንግስት በፊናው የኢትዮጵያ መንግስት ራሱ ጦርነት ልከፍትብኝ ነው በማለት ወንጅሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ እና ለሀገራት መሪዎች በጻፈው ደብዳቤ የኤርትራ መንግስት ጦርነት ለመቀስቀስ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እየጣሰ መሆኑን ገልጿል።

ኤርትራ ለኢትዮጵያ ውንጀላ በሰጠችው ምላሽ፣ ኢትዮጵያ ለጦርነት ባላት ፊላጎት የእኔን ስም እያጠፋች ነው ብላለች። 

የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ላይ በተደጋጋሚ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ከፍቷል፣ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ እና ለሀገራት መሪዎች ደብዳቤን ልኳል፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመጣስ ወንጅሎናል ብሏል የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር።  

ይህ ዓለምአቀፉን ማህበረሰብ የማታለል ጨዋታ እና ለረጅም ጊዜ የተዘጋጀ ወታደራዊ አጀንዳ ነው ያለው።

እውነታው ገዥው ፓርቲ ላለፉት ሁለት ዓመታት የኤርትራን የባህር ወደቦች በኃይል ለመያዝ ስንቀሳቀስ መቆየቱ ነው ብሏል የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር።

ኤርትራ የኢትዮጵያ መንግስት ሰፊ የጦር መሳሪያ ግዥና አውዳሚ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ትላለች።

የኤርትራ መንግስት በቀጠናው የኤርትራን ነፃነትና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ ቢደረግም ትዕግስትን መርጧል ብሏል።

ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን እውነታዎች በማጣመም ኤርትራን ለነጻነቷ አስጊ አድርጋ እያቀረበች እንደሆነ ኤርትራ ተናግራለች።

የኢትዮጵያ መንግስት በአንፃሩ ኤርትራ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ እየገባች ትርምስ ለመፍጠር እየሞከረች ነው ሲል ከሷል።

የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት በተቃራኒ ከቆሙ የውስጥ ሃይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር የሀገሪቱን ደህነት አደጋ ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል በማለት የኢትዮጵያ መንግስት ከሷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቅርቡ የኤርትራ የነጻነት ቀን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር በኦሮሙማ/ኦሮሞነት ላይ ማነጣጠሩ ከፍተኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል።

ኦሮሙማ/ኦሮሞነትን እንደ ርዕዮተ ዓለም አቅርበው ነበር ፕሬዚዳንት ኢሳያስ።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በዚህ አላበቁም የኢትዮጵያን ሕዝብ በኩሽና ሴማዊነት በመከፋፈል ሲናገሩም ተደምጠዋል።

ይህ አካሄዳቸው በኢትዮጵያ ክፍፍል ፈጥረው የፈለጉትን ግብ በቀላሉ ለማሳካት ያለመ ነው ይላሉ የፖሊቲካ ጠበብቶች። 

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ኦሮሙማ/ኦሮሞነትን አስመልክተው የተናገሩት ንግግር ከኦሮሞ የፖሊቲካ ካምፕ እና ከሰፊው ህዝብ ውግዘትን አስተናግዷል፣ ከፍተኛ ቁጣንም ፈጥሯል።

ከ80 በላይ የኦሮሞ ምሁራን ባወጡት ያጋራ መግለጫ የፕሬዚዳንት ኢሳያስን ንግግር በብርቱ ተችተዋል፣ አውግዘዋልም። የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን ጨምሮ አበይት የኦሮሞ ፖሊቲካ ድርጅቶችም የፕሬዚዳንቱን ንግግር አጥብቀው ነቅፈዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ በምርጫ ቦርድ ዕውቅናው የተሰረዘውን ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)ን በሊቀመንበርነት የሚመሩት ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ሰሞኑን በክልሉ ሰማእታት መታሰቢያ ላይ ባደረጉት ንግግር በትግራይ እና በኤርትራ ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት የማጠናከር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ይህን ከተናገሩት ከጥቂት ቀናት በኋላ በትግራይ እና በኤርትራ መካከል የተዘጋው ድንበር ለህዝብ ክፍት መሆኑ ተዘግቧል።

የቀድሞ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጥቂት የህወሓት እና የትግራይ ሃይሎች አመራሮች ከኤርትራ መንግስት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ደጋግመው መናገራቸውም ልብ ይለዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አሰተዳደር ፕሬዚዳንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ የስልጣን ርክክብ ስነ ስርዓታቸው ላይ ከውጭ ሃይሎች ጋር የሚደረግ ያላግባብ ግንኙነት እንደሚያስቆሙ በዲፕሎማቶች እና በባለስልጣናት ፊት የቃልኪዳን ሰነድ መፈራረማቸውም አይዘነጋም።

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ያፈነገጠው የትግራይ ፖለቲካ ቡድን ከኤርትራ መንግስት ጋር ጥምረት በመፍጠር እና በአማራ ክልል ከአንዳንድ የፋኖ አደረጃጀት ጋር ህብረት ለመፍጠር እየሰራ ነው በማለት ይከሳል።

ከትግራይ ወታደራዊ አመራሮች አንዱ የሆኑት ጄኔራል ምግባይ ሃይሌ ለፋኖ ሃይሎች ተልእኮ ሰጥተው አሰማርተዋል፣ ተልእኮውን አክሽፋያለሁ በማለት ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግስት በግልፅ ተናግሮም ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ካፈነገጡ የትግራይ ሃይሎች ጋር ጥምረት መፍጠር ላይ በፋኖ ሃይሎች መካከል ልዩነት መፈጠሩን ምንጮች ገልጸዋል።

በዚህም ከቅርብ ሳምንታት በፊት የተፈጠረው ህብረት ተመልሶ መፍረሱን ሰምተናል።

የጎንደር ፋኖ ሃይል ከወልቃይት እና ከጸገዴ/ጠገዴ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከትግራይ ሃይሎች ጋር መስራት ከባድ ነው በማለት አቋም መያዛቸው ተነግሯል።

የጎጃም ፋኖ በበኩሉ ካፈነገጡ የትግራይ ሃይሎች ጋር ህብረት ለመፍጠር ፍላጎት አሳይቷል። 

በዚህም በጎንደር እና ጎጀም ፋኖ መካከል ከፍተኛ ልዩነት ተፈጥሯል ነው የተባለው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ የትግራይ እና የአማራ ክልሎች በወልቃይት እና በጸገዴ/ጠገዴ ጉዳዮች ላይ ውጥረት ውስጥ ባሉበት የጎጃም ፋኖ በመንግስት ላይ የተለየ ዘመቻ እከፍታለሁ ሲል መግለጫ አውጥቷል።

በእነ እስክንድር ነጋ የሚመራው ሌላው የፋኖ አደረጃጀት በበኩሉ በኤርትራ የፋኖ ታጣቂዎች ለማሰልጠን፣ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለማግኘት እና አደረጃጀቱ በኤርትራ ቢሮ ለመክፈት ይቻል ዘንድ የልዑካን ቡድን ወደ አስመራ ለመላክ መልእክት ስለዋወጥ ከዚህ ቀደም መረጃ አፈትልኮ መውጣቱም አይዘነጋም።

በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ነገሮች እንዲህ እነሰዲህ እያሉ ቀጥለዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ጦርነት እንዳይቀሰቀስም ስጋት ተፈጥሯል።

Show More

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

18 + 4 =

Back to top button
Copy link