AmharicNewsNews Analysis

በኢትዮጵያ ብሮድካሲቲንግ ኮርፖሬሽን ውስጥ ግለሰቦች ተደራጅተው ከፍተኛ ምዝበራ እየፈጸሙ ነው!

"ድርጅቱ የህልውና አደጋ ተጋርጦበታል"

በኢትዮጵያ ብሮድካሲቲንግ ኮርፖሬሽን ውስጥ ግለሰቦች ተደራጅተው ከፍተኛ ምዝበራና ዘረፋ እየፈፀሙ መሆናቸውን ውስጠአዋቂ ምንጮች ገለፁ።

ምንጮች የላኩልን ሰነዶች በደርጅቱ ውስጥ እየተፈፀመ ያለው ዘረፋ የተቋሙን ህልውና አደጋ ላይ መጣሉን ያሳያል።

ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቱን በዘመድ አዝማድና የቅርብ ሰዎች ሪኮመንዴሽን በሚል ኢፍትሐዊ አሰራር እየሞሉት ነው ብለዋል።

በኢቢሲ ከፍተኛ የሥነ ምግባርና የሙስና ወንጀሎች በተደራጁ አመራሮች እየተፈፀመ ይገኛል ያሉት ምንጮች፣ የመንግስት ሀይባይነት ያጣውና በተደጋጋሚ ኢቢሲ እንዲስተካከል ለበላይ አመራር ቦርዶችና በብልጽግና ዋና ጽ/ቤት ውስጥ ለሚገኙና ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ እንዲያደርሱ ቢነገራቸውም የተነገራቸውን መረጃ በሙሉ መንግስት ሰምቶ ችግሩን እንዲፈታ ከማድረግ ይልቅ ለኢቢሲ ዋና ስራአስኪያጅ ለአቶ ጌትነት ታደሰ በመንገር በኮርፖሬሽኑ ውስጥ ተረጋግተን እንዳንሰራ አድርገውናል ብለዋል፡፡ 

በዋና ስራአስኪያጁና በእሳቸው መዋቅር ድርጅቱ የህልውና አደጋ ተጋርጦበታል ነው ያሉት።

የመንግስትን ሥራ አለአግባብ በመምራት ለምዝበራ ምቹ በሆነ መንገድ ለአንድ ሰው ሥራው የማይመለከተው ለአቶ ማማሩ ተስፋ  እስከ ብር 600ሺህ ብር ሥራ ማስኬጃ እንዲሁም ለወ/ሪት ሰናይት ሀይሌ ብር 425,000 በመስጠት ግለሰቦቹ የሚያቀርቡት ደረሰኝ የሪፎርም ሥራ ስለሆነ ማንም ማጣራት እንደለሌበት መመሪያ በአቶ ሞላልኝ መለሰ ትእዛዝ ለሁሉም ሥራው የሚመለከታቸው በመስጠት ሂሳቡ እንዲወራረድ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

በኮርፖሬሽኑ ውስጥ ባሉት ማኔጅመንት አባላት በውሎ አበል ስም ለተለያዩ ወጪዎች መሸፈኛ እየተባለ ከፋይናንስ ሥራ አስፈፃሚ ከአቶ ደረጄ ዳዲ ጀምሮ በየወሩ እስከ ብር 40,000.00 ድረስ ወጪ በማድረግ እያወራረዱ እንደሚገኝ ሰነዱ አመላክቷል፡፡ 

ስምንት የዲቪዥን ኃላፊዎች ኮርፖሬሽኑ በኤሌክትሪክ የሚሰራ መኪና ሰጥቶአቸው ያለመመሪያ ከየካቲት ወር 2017 ጀምሮ በየወሩ የ250 ሊትር የቤንዚን ዋጋ ብር 24500.00   እየወሰዱ መሆናቸው ያስረዳው ሰነዱ፣  ስም ዝርዝራቸውም   ደረጄ አለማየሁ የፋይናንስ ሥራ አስፈፃሚ፤ ሞላልኝ መለሰ የዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ኃላፊ፤ ደረጄ ዳዲ የሰው ሃብት ሥራ አስፈፀሚ፤ ነቢዩ ወንድወሰን፤ ጌትነት ታደሰ ዋና ሥራ አስፈፀሚ፤ ገናናው ለገሰ ሌሎች መሆናቸውን ጠቅሷል።

በሌላ በኩል ሶስት ባህላዊ ጎጆ ቤቶችን ለመገንባት በፕሮፎርማ ግዥ ብር 29 ሚሊዮን ወጪ የተደረገ መሆኑን ሰነዱ አስረድቷል።

ከዚህ በተጨማሪ በሕጋዊ አለም አቀፍ ጨረታ መገዛት የነበረባቸው የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ግዥ ዱባይ ከሚገኙ ደላላዎች በብር 687ሚሊዮን ወይም 5.6 ሚሊዮን ዶላር  በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ግዥ ለመፈፀም  ታስቦ ከውስጥ ጉዳዩ ይመለከተናል ብለው በሥራው የተፀፀቱ የሥራ ኃላፊዎች ከሥራ እንኳን ቢባረር ይሻለኛል በማለት ለሚመለከተው ጥቆማ ሰጥቶ ምርመራ ከተካሄደ በኃላ እንዲቆም ቢደረግም አሁንም በተመሳሳይ መንገድ ከሚያውቁት ድርጅቶች የግል ጥቅማቸውን በሚያስከብር መልኩ ድርድር በማደረግ ላይ መሆናቸውን አስረድቷል።

ከዚህ በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈትቤት ከ2011 ጀምሮ በማንኛውም  በበጀት በሚተዳደሩትና በውስጥ ገቢያቸውና ከመንግስት ከሚሰጣቸው ድጋፍ በሚተዳደሩ አስፈፀሚ አካላት ላይ ያለ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፈቃድ የውጭ ጉዞ ክፍያ እንዳይፈፀም የተላለፈውን መመሪያ በመተላለፍ  በዋና ሥራ አስፈፀሚ ጽ/ቤት ኃላፊ በአቶ ሞላልኝ መለሰ ፈቃጅነት፣ ለዱባይ ከደላላዎች ለቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ግዥ ፕሮፎርማ ማሰባሰብ ለስድስት ኃላፊዎች  1. አቶ ሞላልኝ መለሰ 2. አቶ በለጠ እሱባለው 3. አቶ ማማሩ ተስፋ   እና ሌሎች አመራሮች  ለእያንዳንዳቸው 4700 ዶላር በድምሩ  28,200 ዶላር  ከግል ባንክ በመፍቀድ ወጪ ማድረጋቸውን ጠቅሷል።

ለራሺያና ለቻይና ጉዞ  ለአቶ ጌትነት  የ17 ቀናት  በቀን 4590 ዶላር ከግል ባንክ አካውንትና መንግስት የፈቀደውን የ4ቀናት ጉዞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000 ዶላር መከፈሉን ሰነዱ ያስረዳል።

በቻይና መንግስት ለሥልጠና ሁለት ሠራተኞችን ሙሉ ወጪያቸውን ሸፍኖ እያለ  ከግል ባንኮች 10,600 ዶላር መከፈሉ ያስረዳው ሰነዱ፣ የቻይና መንግስት ለሁሉም ተቋማት ባዘጋጀው የ12 ቀናት ሙሉ ወጪ  ሸፍኖ እያለ ለአምስት  በምክትል ማእረግ ያሉ  1. ሰናይት ሀይሌ 2. አሰፋ በቀለ 3. ታሪኩ ብርሃኑ 4. መሀመድ አወል 5. ፍቅሩ ካሳ ያለአግባብ ለእያንዳንዳችው በአቶ ሞላልኝ መለሰ ፈቃጅነት  ከመንግስት አካውንት ባለመፈቀዱ ከግል ባንክ 23,400 ዶላር ክፍያ መፈፀሙን ይገልፃል።

ወደ ጣሊያን ጉዞ ለአራት ሰዎች 1. አቶ ሞላልኝ መለሰ 2. አቶ በለጠ እሱባለው 3. አቶ አብዱራሂማን ሩቤ  4. አቶ ፍቃዱ ገሰሰ  ያለ ጠቅላይ ሚኒስቴር የውጭ ጉዞ ፍቃድ ተጉዘው  በዚያው ሶስቱ ከአቶ ፍቃዱ ገሰሰ በስተቀር ጌትስአይር ከሚባል የአሜሪካን ኩባኒያ ግብዣ ተደርጎላቸው ወደ አሜሪካ ጉዞ በለመፈቀዱ በአጋጣሚ ከጣሊያን ወደ አሜሪካ በረራ በማድረግ ደርሶ መመለሳቸው ለዚሁ ጉዞ ከብር 10,000,000.00 በላይ ወጪ መደረጉን ሰነዱ ያስረዳል።

የክልል ስቱዲዮ ግንባታ እየተባለ ግልጽ ጨረታ ወይም በውስን ጨረታ እንኳን ሳይካሄድ ለአሶሳ፤ ለጂማ፤ ለወላይታ ሶዶ፤ ለሰመራ ፤ ለጅግጅጋ እና ለዳውሮ ተርጫ በፕሮፎርማ ብቻ ከብር 107 ሚሊዮን በላይ በአንድ አመት ውስጥ የተፈፀመ  ሲሆን  ለግዥ እንዲያመቻቸው በአንድ ግዥ እስከ ዘጠኝ መቶ ሺህ ብር እየቆራረጡ ግዥዎች መፈጸሙና ስቱዲዮዎቹም በገለልተኛ አካላት ኦዲት ቢደረግ አንድም መሳሪያ የሌለውና ለምርቃት ብቻ በሠራተኛው ዘንድ የጎደፈ ስማቸውን ለመገንባት ከዋናው መ/ቤት መሳሪያዎቹን በመንቀል ካስመረቁ በኃላ ወደ ቦታው የሚመልሱት መሆኑን ገልጿል።

 ከዚህ በፊት ተገዝቶ ገብቶ ከነበሩት 25 ካሜራዎች ውስጥ በአንድ አመት የሥራ ቆይታ እንኳን ሳይኖራቸው 12 ተበላሽተው ያለ ሥራ መቀመጣቸው ከእነዚህ ውስጥ በቢሮ  ውስጥ መጥፋቱ ተረጋግጦ እያለ ርምጃ አለመወሰዱን ጠቅሷል።

የአቶ ጌትነት ታደሰ ኔትዎርክ ኮርፖሬሽኑን ማሰራት አለመቻሉንና የመንግስት ሀይባይነት መታጣቱና አቶ ጌትነት ታደሰ በራሳቸው ሾፌር  ስድስት መኪኖች ከንብረት አስተዳደር ወጪ አድርገው እየተጠቀሙበት መሆኑንና ለእነዚህ መኪኖች ነዳጅ በሙሉ ከኮርፖሬሽኑ መሆኑን ሰነዱ  ያስረዳል።

ለኃላፊዎች ለሰርቪስ አገልግሎት የሚሆኑ ስምንት የኤክትሪክ መኪኖች ሲገዙ  የገበያ ዋጋቸው ብር 3,200,000 ሆኖ እያለ በብር 4,200,000.00 መገዛቱን ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ በአቶ ሞላልኝ መለሰ መሪነት የኮርፖሬሽኑ ሠራተኛ ላልሆኑ  13 ግለሰቦች ፓስፖርት እንዲያወጡ በማድረግ ከአገር እንዲወጡ ማደረጋቸውን ሰነዱ ያስረዳል።

የኮርፖሬሽኑ ውስጥ ኦዲተሮች ከ2016 ጀምሮ ያሉትን ወጪዎች ኦዲት እንዳያደርጉና የወጪዎቹን ሚስጢር እንዲጠብቁ ማስጠንቀቂያ በአቶ ሞላልኝ መለሰ በኩል ተስጥቶአቸው ምንም አይነት የግዥ ወጪዎች ኦዲት እንዳያደርጉ  እንዲሁም ሥራ እንዳይፈቱ  በተሰብሳቢ ገቢዎችና ከ2004 ጀምሮ ያሉትን ሰነዶች ኦዲት አድርገው ባለፈው የአመራር ዘመን ችግሮች ነበሩባቸው ብሎ እንዲያቀርቡ ለአቶ ብርሃኑ ቻላቸው  በአቶ ሞላልኝ መለሰ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ተስጥቶ ይህ ሚስጢራዊነቱ መጠበቅ እንዳለበት አስጠናቅቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ያለ አግባብ የአንድ ኣካባቢ ሰዎችን ብቻ የመንግስትን ፖልሲ በምፃረር መንገድ ከ172 በላይ በአንድ አመት ውስጥ ቅጥርና ዝውውር የፈፀመ መሆኑን ውስጠአዋቂዎች በላኩት የስም ዝርዝር አስረድተዋል።

Show More

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

nineteen − 11 =

Back to top button
Copy link